በዳግም ተረፈ እና ማንያዘዋል ጌታቸው
የ43 አመቱ አቶ እንዳለው ተገኝ በሰሜን ኢትዮጵያ አማራ ክልል በባህር-ዳር ዙርያ በርበሬ ፣ ጤፍ፣ ቲማቲም እና ጎመን ለማምረት ለዓመታት በቋሚ የክረመት ዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል።
ይሁንና ባለፍት ጥቂት ዓመታት, ባልተረጋጋ የዝናብ ሁኔታና የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ጥሩ ምርት ሊያገኝ አልቻለም። የጥቁር አባይ ወንዝ ምንጭ በሆነው በጣና ሀይቅ ዳርቻ የሚኖረዉ አቶ እንዳለው በበጋ ወቅትም ሰብል በማምረት ከፍተኛ ለውጥ ለማድረግ ወስኗል። እናም በአሁኑ ጊዜ በበጋ ወቅት በሚሰራዉ የግብርና ስራ ሰባት አባላት ያሉትን ቤተሰቡን ከማስተዳድም ባለፈ የሚተርፈዉን ምርትም ለገበያ ለማቅረብም እየቻለ ነው።
ይህ በመንግስት አነሳሽነትና እገዛ የሚመራዉ የበጋ የግብርና ስራ አርሶ አደሩ ለእርሻ መሬቱ ከጣና ሀይቅ ውሃ እንዲያገኝ በማድረግ ከክረምት የዝናብ ወቅት በበለጠ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ አስችሎታል። የተደረገዉ የአመራረት ለዉጥም የሚያወጣዉን ጉልበትና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲቆጥብም የሚያስችለዉ ነዉ።
“የክረምቱንና የበጋዉን ግብርና ሳወዳድር የበጋው የእርሻ ስራ ከሁለት እጥፍ በላይ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንደማስበው በክረምት በከባድ ዝናብ ምክንያት ምርቱ በጣም ትንሽ ይሆናል። በሁለቱም ወቅቶች የጤፍ፣ የድንች፣ የጎመን እና የቲማቲም ምርቶችን በማፈራረቅና በማምረት ፈትሸን ልዩነቱን ተገንዝበናል። የክረምቱ ምርት ከፍተኛው ነው” ብሏል አቶ እንዳለው።
ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል ላለፉት 9 ዓመታት በክልሉ ሲሰራ የነበረዉ አቶ ብርሃን ጥላሁን አንዱ ነው። እንደ አቶ ብርሃን ገለፃ የበጋዉ የኩታ ገጠም የግብርና ልማት የአማራ ክልል ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ነዉ የሚካሄደው።
አቶ ብርሃን እንደሚለዉ የክላስተር የግብርና በአንድ የተወሰነ መሬት ላይ ከ30-60 ወይም 60-120 አርሶ አደሮችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አንድ አይነት ሰብል ማልማት ሲሆን ተመሳሳይ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይ እና የመስኖ ዘዴዎችን በመጠቀም ቤተሰቦች የተሻለ የግብርና ምርታማነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው።
በዚህ ኩታ ገጠም ፕሮግራም መንግስት ከበርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ለገበሬዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣል። አርሶ አደሮችን በአንድ የተወሰነ መሬት ላይ በኩታ ገጠም በቡድን በማሰባሰብ እና የምርት ብክነት እንዲቀነስ ፣ ተመሳሳይ የሰብል አይነቶችን እንዲዘሩ እና ማዳበሪያዎችንም በተመሳሳይ መልኩ እንዲጠቀሙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸዉ እንዲጨምር ይሰራል። ለምሳሌም በ “ኤስ∙ኤን∙ቪ-ሆርቲ-ላይፍ [SNV-Horti-Life] ፕሮጀክት አማካኝነት በርካታ ገበሬዎች ድጋፍ እያገኙ ይገኛሉ።
“በመጀመሪያ በመስኖ መልማት የሚችሉ መሬቶችን መርጠን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዳሰሳ ጥናት አደረግን። ጥናቱን ተከትሎ ወደ ተግባር ገብተናል። በትግበራው ምዕራፍ ለገበሬዎች የመስክ ዩኒቨርሲቲዎችንም አቋቁመናል። አርሶ አደሮቹ በሳምንት አንድ ጊዜ ተገናኝተው በክላስተር እርሻ ዙሪያ ግንዛቤ ለመጨመር የሚያስችለና የተሻሻሉ የዘር አይነቶችን መጠቀም የሚያሰችሉ ዉይይቶችን ያደርጋሉ።” ሲሉ በኤስ∙ኤን∙ቪ-ሆርቲ-ላይፍ የፕሮጀክት ኦፊሰር የሆኑት አቶ በላይ አለባቸው ተናግረዋል።
የአቶ እንዳለው የእርሻ መሬትም እንቅስቃሴ በአሁን ጊዜ በጣም ሞቅ ያለ ሲሆን በበጋዉ ወቅትም በመስኖ በታገዘ ስርዓት ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ጎመን ሲያመርት ቆይቷል። “በጣና ሀይቅ አካባቢ እስካለን ድረስ የውሃ አቅርቦት ችግር የለብንም። ውሃውን ከሀይቁ ወደ መሬታችን የምናቀርበው የሸራ ፓይፕ በመጠቀም ነው” ይላል አቶ እንዳለው። መንግስት ለአርሶ አደሩ ነዳጅና የሞተር ፓምፕ እንዲያቀርብም ጠይቋል።
የውሃ ፓምፖች እና ቧንቧዎች አቅርቦት ፣የቦይ ግንባታ እና የመስኖ ግድብ ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ ከፍተኛ ችግር አለ። ነገር ግን የአማራ ክልል ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ የውሃ ሃብት አጠቃቀመ እንዲሻሻልና በመስኖ የታገዘ የእርሻ ስራ እንዲካሄድ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ እየሰራ መሆኑን አቶ ብርሃን ገልጸዋል።
ኃያሉ አባይ ከምንጭነት እስከ ወንዝነት
ናይል (ወይም ‘አባይ’ በአማርኛ) የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ነው። ከደቡብ ወደ ሰሜን አፍሪካ 6,695 ኪሎ ሜትር ይፈሳል። የናይል ተፋሰስ ሁለት ዋና ዋና ገባር ወንዞች ያሉት ሲሆን እነሱም ነጭ አባይ እና ጥቁር አባይ ሲሆኑ እነሱም በአስራ አንድ ሀገራት በአጋርነት ስር ያሉ ናቸው። ሀገሮቹም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (ዲ∙አር∙ሲ) ናቸው።
የነጭ አባይ የሚመነጨዉ በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ በታላላቅ ሀይቆች ክልል በኡጋንዳ ዉስጥ ከሚገኘዉ ቪክቶሪያ ሀይቅ ነዉ። ከዚያ በመነሳት በታንዛኒያ እና በኬንያ በኩል በማድረግ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ይፈስሳል። የብሉ ናይል/ጥቁር አባይ/ ወንዝ ደግሞ መነሻው ከኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ነዉ። ሁለቱ ታላላቅ ገባር ወንዞች ሱዳን ላይ ተገናኝተው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ግብፅ ይፈሳሉ ከዛም ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ይገባሉ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 70 በመቶው የኢትዮጵያ ታዳሽ የገጸ ምድር ውሃ የሚመነጨው በአባይ ተፋሰስ በኩል ሲሆን 86 በመቶው የናይል ወንዝን ዓመታዊ ፍሰት ከዚህ ተፋሰስ ይገኛል ።
ላለፉት ሺህ አመታት ኃያሉ የናይል ወንዝ (አባይ) ታላላቅ የአፍሪካ ስልጣኔዎችን እንዲፈጠሩ ያስቻለ ሲሆን እና በተፋሰሱ ሀገራት መካከልም ያለመግባባቶች ምክንያት ሲሆን ቆይቷል። ብዙ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች በወንዞች ዳርቻ እንደተፈጠሩ የዓለም ታሪክ ያስታውሰናል። ለምሳሌ የሜሶፖታውያ ስልጣኔ በቲግሪስ/ኤፍራጥስ ወንዞች ላይ ፣ የጥንታዊ ቻይናውያን ስልጣኔ ደግሞ በ Yellow/ቢጫ/ ወንዝ ላይ እና የጥንቷ ህንድ ስልጣኔ በኢንዱስ ወንዝ ዙሪያ እንደተፈጠሩት የግብፅ፣ የአክሱም ወይም የአቢሲኒያ (የአሁኗ ኢትዮጵያ) እና የኑቢያ (የአሁኗ ሱዳን) ጨምሮ ግዙፍ የአፍሪካ ሥልጣኔዎች ደግሞ በአባይ/አባይ ወንዝ ዙሪያ ተመስርተዋል።
ይህ ኃያሉ የናይል/አባይ ወንዝ በረሃማ የሆኑትን የግብፅን እና የሱዳንን አካባቢዎች ወደ ለምለም የእርሻ መሬትነት ለመቀየር የመስኖ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በንፅፅር የተቀሩት 9ቱ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ግን እስከዛሬ የናይል ውሃ በጣም በትንሹ (ወደ 2% ብቻ) ለመስኖ ልማት ተጠቅመዋል።
የናይል ተፋሰስ፣ ካለዉ ውጣ ውረድ ባለፈም በተፋሰሱ ወሰን ውስጥ ለሚኖሩ ከ272 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኑሮ መሰረት መተዳደሪያ ፀጋ ነው። የአለም ባንክ የ2020 መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ህዝብ ቁጥር 539.2 ሚሊየን እንደሆነ ይገመታል። ከዚህም ዉስጥ የኢትዮጵያ 115 ሚሊየን ሲሆን የግብፅ ደግሞ 102.3 ሚሊየን ነዉ።
በበጋ መስኖ የታገዘ የኩታ ገጠም ግብርና ለአየር ንብረት ለዉጥ አዳፕቴሽን
በክርስትና ምልክትነት የሚታወቀዉን የአንገት ሀብል ያደረገችዉና በጉንጯና በግንባሯ ላይ መስቀል የተነቀሰችው ጠንካራዋ ሴት ሰማሽ አላመር ረዥም ቀሚስ ለብሳ የእርሻ መሬቷን ለቀጣይ የምርት ዘመን በማዘጋጀች ላይ ነች። በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኘው አነስተኛ የእርሻ መሬቷ ላይ በቆሎ፣ ስንዴ እና ቲማቲም ታመርታለች። የ48 ዓመቷ ሰማሽ አምስት የቤተሰብ አባላት አሏት።
እ.ኤ.አ. በ2007 በዝናብ ወቅት 2,395,862 ሰዎች ተጠቂ እንዲሆኑ እንዲሁም 73,746ቱ እንዲፈናቀሉ በማድረግ በ6 ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፣ በትግራይ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ ታስታዉሳለች።
በወቅቱ የዘመዶቻችን ቤቶች መፈራረሳቸዉን ፣ ሰብሎች መዉደማቸዉን እና በጎርፍ መጥለቅለቃቸዉን አስታውሳለሁ። በዚህ ምክንያት ተፈናቅለዋል ፣ እራሳቸውንም መመገብ አልቻሉም እና በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሆነዉ ነበር። ” ስትል ሰማሽ ተናግራለች።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋናነት በግብርና ላይ የተመሰረተ ሲሆን ይህም የሰብል እና የእንስሳት ምርትን ይጨምራል። ዘርፉ ለ45 በመቶ አገራዊ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP)፣ ከ80 በመቶ በላይ የስራ እድል ፈጠራ እና ከ90 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም የግብርናዉ ልማት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የወጪና ገቢ ምርቶች ዓለም አቀፍ ዋጋ መለዋወጥ ባሉ ምክንያቶች እጅግ በጣም የሚናጋ መሆኑን የ2020 የጂ∙አይ∙ዜድ ጥናት ያሳያል።
“የእኔ አዝእርቶች በክረምት ወቅት በጎርፍ ይጥለቀለቃል። በተለይ ምንም ዓይነት የመከላከያ ግንቦች እና እርከኖች በማይኖሩበት ጊዜ የከፋ ጉዳት አይተናል። መሬታችን ሲንሸራተት፣ ሲታጠብና ገደል እየሆነ ሲሄድ አስተውለናል” ይላል አቶ እንዳለው።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የጣና ሀይቅ ተፋሰሶች በሆኑት በፎገራ እና ሊቦ ከምከም አካባቢዎች ከባድ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ የ25,000 ሰዎች ን ህይወት የነካ ሲሆን 2 ሰዎችን ገድሏል፣ 6,653 ቤቶችን ጠራርጎ ወስዷል፣ 18 ትምህርት ቤቶችን አዉድሟል እንዲሁም እ∙አ∙አ በ2019 ብቻ 3,428 ሄክታር የሚሸፍን የሰብል ወድሟል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የእፅዋት ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ እውነቱ ታከለ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ እንቅፋት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ በሀገሪቱ ያለውን ባህላዊ የግብርና አሰራር እየገደበም መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሚያዝያ ወር የጀመረውና በግንቦት ወር ላይ ጠንከር ብሎ የጣለው ከመጠን ያለፈ ከባድ ዝናብ ጎርፍን፣ መፈናቀልን ፣ የህይወት መጥፋትና የኑሮ መዛባትን አስከትሏል እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች አዉድሟል። በ OCHA (2020) ሪፖርት መሰረት ፣ የጎርፍ አደጋ ከ470,000 በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከ300,000 በላይ ሰዎች አፈናቅሏል ። ከዚህም ዉስጥ 80 በመቶው የሚሆነዉ በሶማሌ ክልል ነዉ።
በ2020 ደግሞ ከተለመደዉ ከፍ ያለ ዝናብ በመጣሉ የናይል ወንዝ እና አንዳንድ ገባር ወንዞቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሱዳን ዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ዉድመት አደረሰ። ከጁላይ 2020 አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ የተስፋፋው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ የ100 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ፣ ከ110,000 በላይ ቤቶችንም አፈራርሷል ወይም አዉድሟል።
እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 2022 በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት (WMO) የታተመ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያመለክተው ምሥራቅ አፍሪካ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ የዝና እጥረት ተጋርጦበታል፣ ይህም ባለፉት 40 ዓመታት ተከስቶ በማይታወቅ መልኩ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን እና ሶማሊያን ወደ ድርቅ ችግር ውስጥ ይከታል። በ WMO ትንበያ መሰረት በኢጋድ (IGAD) ክልል ዉስጥ ከ29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ተጋልጠዋል።
የ2022 የአይ∙ፒ∙ሲ∙ሲ ሪፖርት እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በመሬት ይዞታ ፣ በንፁህ ውሃ እና የባህር ዳርቻ እንዲሁም በውቅያኖሶች የባህር ስነ-ምህዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊቀለበስ የማይችል ኪሳራ እያስከተለ ነዉ።
እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ዘገባ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎች በጣም የተጋለጠች አህጉር ነች። በተለይ በላይኛው የናይል ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙት ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ በአየር ንብረት ጽንፍ ምክንያት የእርሻ ስራ መቆራረጥ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት 10 ዋና ዋና የድርቅ ወቅቶችን አስተናግዳለች እና አማካኝ አመታዊ የሙቀት መጠንም በ0.37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በየአስር አመቱ እያደገ ሲሆን አብዛኛው የአየር ሙቀት መጨመርም የተከሰተው በ1990ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ነው።
የዩ∙ኤስ∙ኤ∙አይ∙ዲ የዘላቂ ውሃ አጋርነት መረጃ እንደሚያሳየው በቅርቡ ከ2015-16 የተከሰተው የኤልኒኖ ክስተት በምስራቅ፣ደቡብ እና መካከለኛው ኢትዮጵያ ሰፊ አካባቢዎች ድርቅ ሲያስከትል በሰሜን ምስራቅ እና ማእከላዊ ክልሎች ደግሞ የዝናብ መጠኑ ከአማካኝ ዝቅ ብሎ 65 በመቶ በታች ሆኖ ቆይቷል። በጣም በተጎዱ አካባቢዎች አንድ ሚሊዮን የቤት እንስሳት እና 75 በመቶው የሰብል መሬቶች የጠፉ ሲሆን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም አስቸኳይ እርዳታ ፈላዎች እነዲሆኑ አድርጓል። በዚህ አመት በተደረገ ጥናትም በዝናብ ላይ የተመሰረተው የሰብል ምርት ከ2.1-4.1 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ከ2.4 እስከ 9.7 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 115 ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን በ2050 ከ200 ሚሊየን በላይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በ2050 የአለም ህዝብ ቁጥር ከ9.1 ቢሊዮን እንደሚበልጥ ሲገመት በሚቀጥሉት 40-50 አመታት የሚታየዉ የህዝብ ቁጥር ለውጥም በአብዛኛው ከአፍሪካ እና በአህጉሩ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ላይ በምትገኘዉ ከኢትዮጵያ የሚጠበቅ ነዉ።
“ግብርናችንን ባህላዊ ከሆኑ አነስተኛ ደረጃ ወደ መካከለኛ ወይም በሰፊ መስኖ ስራ የሚታገዝ ከፍተኛ የበጋ ሜካናይዝድ የግብርና ስራ የማሸጋገር እድል ካልተፈጠረ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አንችልም፤ ምክንያቱም በከፍተኛ የህዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት የመሬት እጦት ተጋርጦብናል።” ይላል የግብርና ኤክስቴንሽን መኮንኑ ብርሃኑ።
ያልተመጣጠነ የመስኖ ልማት ስርዓት በናይል ተፋሰስ
“በመስኖ ግብርና ውስጥ የውሃ ቁጠባ ሁኔታ” የተሰኘዉ የ2020 ዓ∙ም∙ የናይል ተፋሰስ ቴክኒካል ሪፖርት እንደሚያመለክተው በናይል ተፋሰስ ውስጥ ካሉት የመስኖ ስርዓቶች 98 በመቶው በግብፅ (58 በመቶ) እና በሱዳን (30 በመቶ) የሚገኙ ሲሆን በተቀሩት 9 የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ 2 በመቶ ያህሉ ብቻ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ መታረስ ከሚችለዉ መሬት 10 በመቶው በመስኖ ሊለማ የሚችል ቢሆንም ከ6 በመቶ ያነሰዉ ብቻ ጥቅም ላይ ይውላል። ሀገሪቱ በዝናብ ላይ የተመሰረተ ግብርና እየተከተለች በመሆኗ ምርታማነት የተገደበ ሆኗል። የአርሶ አደሮችም የድርቅ ተጋላጭነትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖንም ጨምሯል።
ጂ∙አይ∙ዜድ እና ሌሎች የልማት አጋሮች መስኖ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት እና በመጨረሻም በኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ እና ቁልፍ የልማት ግቦችን ለማምጣት አንዱ ቁልፍ መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂና ግብአት ለማያገኙ እንደ ሰማች ላሉ አርሶ አደሮች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት መዘርጋት ግዴታ እንጂ የምርጫ ጉዳይ አይደለም።
“የእርሻ መሬቶቻችን እና ማዳበሪያዎቻችን በክረምት ወቅት በጎርፍ ታጥበው ይባክናሉ; በአንፃሩ በበጋ ወራት እርሻን ማልማት ከቻልን አዝመራችን በጎርፍ እና በበረዶ አይጎዳም ይህም ስለ ጎርፍ ጉዳት ሳንጨነቅ ምርታማነትን ሊያረጋግጥልን ይችላል” ስትል ሰማችሽ ተናግራለች።
እንደአለው እና ሰማችሽ በሚኖሩበት አካባቢ እ∙አ∙አ ከ2021 ጀምሮ የበጋ ሰብል ልማት እየተስፋፋ መጥቷል።
“በክረምት ቲማቲም እያመረትን አልነበረም ነገር ግን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ስላደረጉልኝ ቲማቲም አምርቼ 35,000 ብር አግኝቻለሁ። እኔ ተጠቃሚ ነኝ እና አሁን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ወጥቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ሌሎችም የኔን ፈለግ ተከትለው ወደ በጋ እርሻ እየገቡ ነው” ትላለች ሰማችሽ።
“ምንም እንኳን በክረምት ወቅት ውሃ ከእግዚአብሔር ብናገኝም መጠኑን መተንበይ ግን አንችልም። ይሁንና በበጋ ወቅትም ውሃ እንዲሁም የሰው ኃይል እና የሞተር ፓምፕ እንፈልጋለን” ስትል አክላ ተናግራለች።
ሰማችሽ እና ሌሎች አርሶ አደሮች ለበጋ እርሻ የሚውል ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የመስኖ ፓምፖችንና ቧንቧዎችን መንግስት አንዲያቀርብላቸዉ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ‘ቆጋ’ ን መሰል ግድብ ለመስኖ ስራ እንዲለማላቸዉምጠይቀዋል።
“መንግስት የውሃ ፓምፖችን፣ የተሻሻሉ የፕላስቲክ ቱቦዎችን እና ነዳጅ ለመግዛት ብድር ቢሰጠን የበለጠ ማምረት እንችላለን። የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ምክርና አቅጣጫ እያገኘን ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የደላሎችን የገበያ ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ በአካባቢያችን የገበያ ማዕከል እንዲቋቋም ከመንግሥት ድጋፍ እንፈልጋለን።” ብሏል እንዳለዉ። አሁን በቡና ላይ የምክክርም ሌሎች አርሶ አደሮች የእሱን ፈለግ እንዲከተሉ እየመከረ ይገኛል።
አቶ አለኸኝ እንዳሉትም መካከለኛና ሰፊ የመስኖ ግድቦችን መገንባት ለአርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖ መቋቋም ይረዳል። አሁን ያሉት የመስኖ ግድቦች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል።
“የርብ” መካከለኛ መስኖ ግድብ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሟች አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቢመረቁም ከፌዴራል መንግስት በጀት እጥረት የተነሳ የቦይ መዋቅራዊ ስራዎች እስካሁን አልተጠናቀቁም። ‘መገጭ’ እና ‘ሰርባ’ ግድቦች እንኳን በከፊል እየሰሩ ናቸው” ያሉት አቶ አለኸኝ የግድቦቹ ስራ ከትክክለኛ ስራነት ይልቅ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ እየሆነ ይታያል ሲሉ ተችተዋል።
አቶ አለኸኝ ክንዴ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በአትክልት፣ ፍራፍሬና ሰብል ጥበቃ ባለሙያ በመሆን ይሰራል። መንግስት አርሶ አደሩን በላቁ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መርዳት ቢችል በአማራ ክልል የተረጋጋ የውሃ አቅርቦት በመኖሩ ውጤታማ የበጋ ግብርና ለማድረግ ትልቅ አቅም አለ ብሏል።
“በክረምት ወቅት ዝናቡ ሰበል ከመሰብሰቡ በፊት ወይም በኋላ ሊከሰት ይችላል። ከባድ ዝናብ እና ጎርፍም ሊከሰት እና በእርሻ ወቅትም ዘሩን አጥቦ ሊወስደዉ ይችላል” ብሏል።
ይሁንና የዕፅዋት ሳይንስ ባለሙያው አቶ እውነቴ እንደሚለዉ በበጋ የክላስተር እርሻ ወቅት አፈርና ማዳበሪያዎች ብዙም ሳይታጠቡ እና ሳይባክኑ ይቆያሉ እናም ንጥረ ነገሮች በአፈር ውስጥ ይያዛሉ።
“በዚህ አመት በመስኖ በታገዘ የክላስተር እርሻ በዘንዘልማና ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳዎች ከፍተኛ የስንዴ ምርት አግኝተናል” ይላል አቶ እውነቱ። ሞዴሉን እስካሁን የሜካናይዝድ የግብርና ስርዓት ወደሌለበት የሮቢት ወረዳ የማስፋፋት አቅም አለ ብሏል።
እ.ኤ.አ. ከ1989 ጀምሮ ከተለያዩ ምንጮች በተጠናከረው የናይል ሀገራት የመስኖ ልማት ትንበያ የNBI መረጃ እንደሚያሳየው የላይኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት አማካይ አመታዊ የመስኖ እድገት መጠን 18 በመቶ ነው። ምንም እንኳን ይህ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሱዳን እና ግብፅ ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍ ያለ ቢሆንም ከዚህ ዝቅተኛዉ መነሻ ጀምረዉ በፍጥነት እያሳደጉት ሊሄዱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ይህ አዝማሚያ እንደ ግብፅ ያሉ የመስኖ አካባቢዎችን እድገት ያሳያል፡ በ1989 ከነበረው 3 ሚሊዮን ሄክታር በ2018 ወደ 6.5 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን ያመለክታል፣ የ 2 በመቶ አመታዊ እድገት ማለት ነዉ፣ የኢትዮጵያን ስናይ ደግሞ በ1989 ከ23,160 ሄክታር የነበረዉ በ2018 ወደ 455,421 ሄክታር ከፍ ብሏል ፣ ይህም 35 በመቶ አመታዊ እድገት ማለት ነዉ።.
የመስኖ ልማት አዝማሚያ፣ ሁኔታ እና ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ (2021) በተሰኘዉና በቅርቡ በተደረገ የጥናት መሰረት ምንም እንኳን በኢትዮጵያ አነስተኛ የመስኖ ልማት ከ2,000 ዓመታት በፊት ምናልባትም በአክሱም ግዛት የተጀመረና ረጅም ታሪክ ያለዉ ቢሆንም መካከለኛና መጠነ ሰፊ የመስኖ ልማት በደንብ በታቀደ መልኩ የተጀመረዉና የተተገበረዉ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ነው።
በአነስተኛ መስኖ የሚለማው መሬት በኢትዮዽያ እ∙አ∙አ በ1991 ከነበረበት 176,105 ሄክታር በ2019 ዓ.ም ወደ በ2.5 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ብሏል። በመጀመሪያዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ፣2010/11 – 2014/15 ፣ የአነስተኛ መስኖ መሬት በ15∙2 በመቶ ሲጨምር የሁለተኛው የእቅድ ዘመን ከ2015/16 – 2019/20 አፈፃፀም ግን እስካሁን ሙሉ በሙሉ ተገምግሞ አላለቀም።
እ∙አ∙አ በ1991 ዓ.ም የመካከለኛና መጠነ ሰፊ የመስኖ ልማት ሙሉ በሙሉ የተጀመረው በውጭ ንግድ ኩባንያዎች በተለይም በመስኖ የሚለሙ የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች ሲሆን በሀገሪቱ በተለይም ባሉ በአዋሽ ተፋሰሶች ወንጂ (5,000 ሔክታር) እና መተሐራ (11,000 ሄክታር) ነበር ። ቀደም ሲል ከ1954 እስከ 1966 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሥራዉ የጀመረው በመንግስት እና በኔዘርላንድ ኩባንያ በሃንግለር ቮንድር አምስተርዳም (HVA) መካከል በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ነበር ።
መርቲ እና ጄጁ (1638 ሄክታር) የጥጥ መስኖ ፕሮጄክት በ1961/62 በጣሊያኑ ሰኢግኒየር ቲሊዮታ ሳንቶ የተመሰረተ ሲሆን በኋላም በ1975 ዓ.ም ወደ መንግስት ባለቤትነት ዞሮ በዉህደት “መርቲ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነዳበሪያ” ተብሎ መሰረተ። መንግስታዊ የነበረዉ የአሚባራ የመስኖ እርሻ ደግሞ መልካ ሰዲ እና መቅላ ወረር (10,000 ሄክታር) እንዲሁም የኑራ ሂራ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ እና የመርቲ አግሮ ኢንዱስትሪን ያቀፈው ድርጅቶች ደግሞ በ1980 እና 1983 በቅደም ተከተል ስራ ጀመሩ።
በ1977 በተከሰተዉ አስከፊው ረሃብ ምክንያት ደግሞ በመንግስት ድጋፍ የአምራች ህብረት ስራ ማህበራት በስፋት በተቋቋሙባቸው ብዙ አካባቢዎች በአነስተኛ የመስኖ ፕሮግራም ልማት ትልቅ ለዉጥ አምጥተዉ ነበር። የዚህም ዕቅድ ግብ 57,000 ሄክታር መሬት ማልማት ነበር ነገር ግን በ1983 በስርዓት ለውጥ ምክንያት የዚህ ዒላማ ስኬት ሳይገመገም ቀረ።
የመንግስት ለውጡን ተከትሎም እንደ “የዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ መርሃ ግብር” /2002-2005/ እና “የድህነት ቅነሳና የተፋጠነ ልማት እቅድ GTP I&II ” ከ2005-2010 እና ከ2010 – 2020 ባሉ በተለያዩ ሀገራዊ የልማት መርሃ ግብሮች በመስኖ ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ።
በአነስተኛ መስኖ የሚለሙ የግብርና ምርቶችን በተመለከተ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ እ∙አ∙አ በ2018 ከ932,743.27 ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቶ 110 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት የተገኘ ሲሆን ይህ በ2019/20 ወደ 220,612 ሄክታር መሬትና 31 ሚሊዮን ኩንታል በታች ምርት ብቻ በመሆን ቅናሽ አሳይቷል።ነገር ግን በ2020/21 መጠነኛ እድገት አሳይቶ ወደ 38 ሚሊዮን ኩንታል ምርትና 325,811.17 ሄክታር የመስኖ መሬት ተመዝግቧል።
ከ2018/19 እስከ 2019/20 ድረስ በመስኖ የለማዉን መሬት እና የምርት መቀነስን በተመለከተ ከሚመለከታቸዉ ባለሥልጣናት ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም።
እ∙አ∙አ በግንቦት 2019 የገንዘብ ሚኒስቴር ከውጭ ለሚገቡ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ መስኖ እና የእንስሳት መኖ ቴክኖሎጂዎችን እና መሳሪያዎችን ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ማድረጉ ይታወሳል።
“የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት አርሶ አደሮች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የግብርና ቴክኖሎጅዎችን እንዲያገኙ የሚያስችል አቅጣጫ ሰጥቷል” ሲል ምክር ቤቱ በድረ-ገጹ አስፍሯል።
የስኳር ኮርፖሬሽንም ለሸንኮራ አገዳ ምርትና ማቀነባበሪያ፣ ለግል ባለሀብቶች ለንግድ ሰብሎች ምርትና ለአነስተኛ ይዞታ እርሻዎች መካከለኛና መጠነ ሰፊ የመስኖ ዘዴዎች እተየዘጋጁም ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ 160,921 ሄክታር የሚጠጋ የሸንኮራ አገዳ ምርት የመስኖ መሬት በማስተዳደር ላይ ሲሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚገኙ ስምንት ፕሮጀክቶች ላይም ተካፋይ ነዉ።
በአጠቃላይ 300,000 ሄክታር መሬት ላይ የሚሸፍን የመስኖ ቦታ በኮርፖሬሽኑ የሚተዳደር ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚተገብረዉ በሀገሪቱ በመካከለኛና በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ነው።
በትብብር እይታ የተቃኘ የጋራ የውሃ ልማት
እንደ ናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ከሆነ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ መጠቀም ለተፋሰስ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና የዉሃ ደህንነታቸዉን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ነዉ።
ከፍተኛ መጠን ባለው ዝናብና የአየር ፀባይ ለዉጥ ምክንያት በላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት ወደ ተፋሰሱ ሀይቆች እና ወንዞች የሚለቀቀዉ ውሃ ከፍተኛ መጠን ያለው ሲሆን ይህንን አከማችቶ በበጋ ወራት መጠቀም ይችላል። ጥቁር አባይ (ብሉ ናይል) በአማካይ 82 በመቶው ዓመታዊ ፍሰቱ ከጁላይ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ውስጥ በአራት ወራት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን የሴቲት ወንዝ ግን 80 በመቶው ፍሰቱ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ እንደሚከሰት የናይል ኢኒሸቲቭ ዘገባ ያሳያል።
ከፍተኛ መጠን ያለው የአባይ ውሃ በትነት ምክንያት ይጠፋል። ይህ በደቡብ ተፋሰስ አገራት በግብፅ እና በሱዳን ከኢትዮጵያ የበለጠ ከፍ ያለ ሲሆን በበጋ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ በቀዝቃዛው ደጋማ ቦታዎች ውስጥ ሊከማች ይችላል ሲል የናይል ኢኒሸቲቭ ጽፏል። በዚህ መንገድ ከሚሰሩት ሰው ሰራሽ ማጠራቀሚያዎች በአማራ ክልል እና በሌሎችም ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ በሚረዳ መልኩ ውሃዉን በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ በመልቀቅ ሰብል እንዲያመርት ያስችላል።
በግብፅ እና በሱዳን ውሀ በከፍተኛ ፍጥነት በሚተንበት ጊዜ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም ከፍተኛ የመስኖ ስራን ምስራት ይመከራል። ግብፅ እና ሱዳን ከሊቢያ እና ቻድ ጋር በዓለም ላይ ትልቁን ታዳሽ ያልሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ይጋራሉ። በውሃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ከተከማቸው ከ500,000 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር በላይ ውሃ ውስጥ 14,818 ኪዩቢክ ኪሎሜትር የሚጠጋው ውሃ ሊገኝ የሚችል ሲሆን በግብፅ 5,525 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር እና በሱዳን 4,787 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር መጠን ያለዉ የከርሰ ምድር ውሃ እንደሚገኝ የናይል ኢኒሸቲቭ ዘግቧል።
የከርሰ ምድር ውሃን ከማውጣት ጎን ለጎን የግድቦችና የውሃ ማጠራቀሚያዎችን መጠን ወይም ቁጥር በመጨመር የማጠራቀሚያ አቅምን በማሻሻል፣ጨዋማ የዉቅያኖስ ውሃን በማጣራትና መጠቀም/ድesalination/ ፣የዝናብ ውሃ ክምችትን ማስፋፋትና የውሃ ሽግግርን መጠቀም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንደ ውጤታማ እርምጃዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።
ይህ መጣጥፍ ኢንፎ ናይል/InfoNile/ ከሚዲያ ኢን ኮኦፐሬሽን እና ትራንዚሽን (MiCT) እና ከናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (NBI) ጋር በመተባበር እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት እና በፌደራል ጀርመን መንግስት በተወከለው በጂ∙አይ∙ዜድ (GIZ) ድጋፍ የቀረበ ነዉ።
The post በሞቃታማው የጥቁር አባይ ምንጭ ዙሪያ ለመኖር የሚደረግ የህልውና ትግል appeared first on InfoNile. InfoNile - Geodata journalism. Mapping stories on water issues in the Nile Basin.